ሱሉልታ፡ 08/12/2017 ዓ.ም
በስልጠና ቦታው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባለፉት 2 ዓመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸዉን ጠቅሰዉ የሰው ኃይል ማሟላት፣ ማልማት ፣ መልሶ ማደራጀት እና መዋቅራዊ ተግባራትን መከናወናቸዉን ለአብነት አንስተዋል። በዚህ ዓመትም የሰው ሀይሉን በስልጠና እና ትምህርት አቅሙን ለማሳደግ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ሰራተኞችን የማሰልጠን ስራ በሰፊው ይከናወናል ብለዋል፡፡
የስልጠናዎቹ ዋነኛ ዓላማ በፅንሰ ሃሳብ እና በክህሎት የዳበረ የሚጠበቅበትን ተግባርና ኃላፊነት ተገንዝቦ የሚመራና የሚሰራ አመራርና ሰራተኛ ማዘጋጀት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተርዋ በ2018 ዓ.ም የተያዘዉን ሰፊ ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ መሰል ስልጠናዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡ በመጨረሻ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ሁሉም ሰልጣኞች የመጡበትን ዓላማ በመገንዘብ ስልጠናውን የሚፈልገውን ትኩረት በመስጠት እና ተቋማችን ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ በማያያዝ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የአመራርነት ስልጠናው ስሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ የልሕቀት አካዳሚ እየተሰጠ ሲሆን ከነሀሴ 08 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ለ6 ቀን የሚቆይ ይሆናል፡፡ በቆይታው በመሪነትና ቡድን ስራ፣ በጊዜ አጠቃቀምና ግጭት አፈታት፣ በውሳኔ ሰጭነትና ችግር ፈቺነት፣ በተቋማዊ መዋቅርና ሪፎርም፣ በሳይበር ሴኩሪቲ፣ በዲፕሎማቲክ ፕሮቶኮልና አለምአቀፋዊ ግንኙነት ወዘተ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
——
