አዲስ አበባ ፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም
የኢ.ፌ.ድ.ሪ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ ጎተራ በሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ቢሮ እየተሰጡ ያሉ የፓስፓርት፣ ቪዛ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የህትመት እና ስርጭት አገልግሎቶችን እንዲሁም የውጪ ዜጎች አገልግሎቶችን ጎብኝተዋል።
የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተርና የኢሚግሬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጎሳ ደምሴ እና የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተርና የዜግነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቢቂላ መዝገቡ በቴክኖሎጅ በመታገዝ ተቋሙ እያከናወነ ያለውን የሪፎርም ተግባራት ለሚኒስትሩ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ አዲሱን የኢ-ፓስፖርት ጨምሮ የቪዛ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ፣ የውጪ ዜጎች መኖሪያ ፈቃድ እና ሌሎች የጉዞ እና የይለፍ ሰነዶችን ዘመናዊና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በሀገር ውስጥ ማምረት በመጀመር ለህትመት ይወጣ የነበረን ወጪ ማስቀረት መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
ሚንስትሩ ተቋሙ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን እና ለስራ ምቹ ከባቢ መፍጠሩንም አድንቀዋል።በሪፎርም ስራ አማካኝነት ወረቀት ላይ የተመሰረተ አሰራርን ወደ ዲጂታል ሥርዓት መሸጋገር መቻሉም ለሌሎች ተቋማት አርአያ እንዲሆን የሚያስችለው ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።
ተቋሙ በቀጣይም የጀመራቸውን የሪፎርም ተግባራት በማፋጠን እና በማስፋት ዜጎች በአገልግሎቱ የሚደሰቱበት እና የሚረኩበት ተቋም ለመሆን የያዘውን እቅድ እውን ማድረግ አለበትም ብለዋል።
