የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

አዲስ አበባ ፡ ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ዘመናዊ እና የተቀላጠፈ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጿል። 

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ እና የስራ ክንውን ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የዜግነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቢቂላ መዝገቡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን አሰራር ዲጅታላይዝ ማድረግ፣ የሰው ሃይልን ማጠናከር፣ የስራ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ እንዲሁም የተንዛዛ አገልግሎትን ማስቀረት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በሁሉም ቅርንጫፎች ያለው አሰራር ወጥነት ያለው እና በተመሳሳይ መልኩ የተቀላጠፈ እና ጊዜውን የዋጀ እንዲሆን የሚያስችል የአገልግሎት አሰጣጥ ማኑዋል  እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። 

በሌላ በኩል አቶ ቢቂላ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በየአቅራቢያቸው የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጡን፣ ደንበኞች ማሟላት በሚገባቸው ሰነዶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማስተማር፣ ከፍትህ እና ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ደግሞ ህገወጦችን የመከላከል ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አቶ ቢቂላ አያይዘውም በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የሚሰሩ አመራሮች እና ባላሙያዎች ከአድሎ የፀዳ እና ከማንኛውም ህገወጥ አሰራር በመራቅ ማገልገል እንደሚኖርባቸው በመግለፅ በታማኝነት፣ በቅንነት እና የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ በመስራት ተቋሙ የያዘውን የተገልጋዮችን ፍላጎት ማሟላት እና እርካታ እውን የማድረግ እቅድ ላይ መስራት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133