በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ በክብርት ወ/ሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ የተመራ የሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን የስራ እንቅስቃሴዎችን ጎበኘ፡፡

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 04 ቀን 2018 ዓ.ም

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አለምጸሀይ ጳውሎስ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት ልኡካን ቡድን በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እየተተገበረ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እየተተገበረ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለልዑካኑ አስረድተዋል። ልኡካን ቡድኑ በቀን 3 ሺህ አስቸኳይ ፓስፖርት ፈላጊ ደንበኞችን ሊያስተናግድ የሚችለውን ማስተናገጃ ቦታ፣ በዘመናዊ መልኩ የተሰራውን የሰራተኞች ካፌ፣ የቪ.አይ.ፒ. እና የውጭ ዜጎች የሚስተናገዱበት ክፍሎችን፣ ደንበኞች ባሉበት ሆነው መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የነፃ ጥሪ ማዕከል፣ የዜጎች አዲሱ ኢ-ፓስፖርትና የውጭ ዜጎች የጉዞ ሰነዶች የሚታተሙበት ዘመናዊ የህትመት ማሽኞች የያዘ ክፍሎችን ጎብኝተዋል፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ በጉብኝቱ ወቅት ሲገለገሉ የነበሩ ደንበኞችን ያነጋገሩ ሲሆን ግልፅነት በተሞላበት እና በፈጣን አገልግሎት እንደተስተናገዱ ተገልጋዮቹ ለልኡካን ቡድኑ ገልፀውላቸዋል፡፡ 

ልዑካን ቡድኑ በተቋሙ እየተከናወነ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለሌሎች ተቋማት ተምሳሌት የሚሆን መሆኑን ገልጸው በተደረገላቸው ገለጻ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ በፊት ከነበረው ሁኔታ አንፃር ትልቅ ለውጥ መኖሩን አውስተዋል።

በአገልግሎቱ የበላይ አመራሮች ገለፃና ማብራሪያ የተደረገላቸው የልኡካን ቡድኑ አባላት አጠቃላይ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እየተከናወነ ያለውን የሪፎርም ስራዎችን በማድነቅ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 

በክብርት ወ/ሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ የተመራው ልኡካን ቡድን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲኦን ጢሞቲዎስ፣ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከማል እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ያካተተ ነው፡፡

ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133