የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ዛሬ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም በቂሊንጦ ኢንደስትሪያል ፓርክ ውስጥ “የምትተክል አገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል 3000 ችግኞችን ተክለዋል።






በስነ-ስርዓቱ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት አገራችን ባለፉት 6 አመታት ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመትከል በዓለም የራሷ አሻራ ማስቀመጧን አስረድተው የዘንድሮ ችግኝ ተከላ ኘሮግራምም በሀገር አቀፍ ደረጃ “የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የተከላ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞችም 3000 የሚሆኑ ለምግብነት የሚውሉ (የማንጎና አቨካዶ) ችግኞችን በመትከል የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ገልፀው እነዚህ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ከአረንጓዴ አሻራና አየር ንብረት ሚዛን ከመጠበቅ በተጨማሪ አገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው እንቅስቃሴ የራሱ አወንታዊ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

አክለውም ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ከፀደቁ በኋላም ቀጣይነት ባለው መልኩ መንከባከብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሠራተኞች የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 2 ሚሊየን ብር እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሰጥ በመወሰን በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በአገልግሎት ተቋሙ ስም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
