የኢ-ፖስፖርት፣ የክፍያ ካርዶች እና መታወቂያዎች ማምረቻ ፋብሪካውን ግንባታ ለማስጀመር ከኢትዬጵያ ኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት በተገኘ ቦታ በለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ መሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ኢ-ፓስፖርት በሀገር ዉስጥ መመረቱ ከሚያስገኘዉ ጥቅም ባሻገር አዲስ እዉቀትና ቴክኖሎጅ ወደ ሀገር የሚያስገባ እንደመሆኑ መንግስት አስቀደሞ ያለዉን ችግር በመገንዘብ በተለይ ከጊዜዉ ቴክኖሎጅ ጋር አብሮ መሄድ እንዲቻል የተሰራዉ ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑን በመግለጽ በአዲሱ የኢ-ፓስፖርት የሀገራችን የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን እንዲሁም ታሪካዊ ስፍራዎችን ጨምሮ የበለፀጉ የደህንነት መገለጫዎችን የያዙ አዳዲስ ዲዛይኖችን እንዲካተቱ የተደረገ ሲሆን ይህ ፕሮጅክት በአገራችን ዉስጥ ለረዥም ጊዜ የቆየዉን የፓስፖርት እጥረት ለመፍታት ፣የደንበኞችን እርካታ ለማሻሻልና በፍተሻ ጣቢያዎች ይጠፋ የነበረዉን ጊዜ ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡




በተጨማሪም ሀገራችን ወደ ኢ-ፓስፖርት መግባቷ ቀደም ሲል ባለፉት ዓመታት ስንጠቀምበት የነበረዉን ፓስፖርት ደረጃውን ከፍ ያደረገ ብቻ ሳይሆን የዲዛይን ባለቤትነትም ወደ ሀገር የተመለሰበት እንዲሁም የዳታና የፕሮሰሲንግ ስራ በራስ አቅም እንዲሰራ መንገድ የተከፈተላትም ሲሆን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚሰጣቸዉ ጊዚያዊ እና ቋሚ የመኖሪያ መታወቂያ፣ የትዉልደ ኢትዬጵያዊ መታወቂያ እንዲሁም ሌሎች መታወቂያዎች ከወረቀት ወደ ዲጅታል እንዲያድጉ ከመደረጉም በላይ የቪዛ አዉቶሜሽንም አብሮ እንዲሰራ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ይህ ለፍሬ እንዲበቃ የዲዛይን ስራዎችን፣ የህግ ስራዎችን እና አጠቃላይ ስራዉን ከመጀመር አንስቶ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ የተሳተፉትን ክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተቋምን፣ የJoint venture CEO የሆኑት ወ/ሮ ቃልኪዳንን እንዲሁም የቶፓን ግራቪቲ የስራ ኃላፊዎችና ባልደረቦችን አመስግነው በቀሩት ወራት በጋራ በመስራት አዲሱን የኢ-ፓስፖርትም ሆነ ፋብሪካዉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የበኩሉን ድጋፍና የሚጠበቅበትን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
