በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በጅዳና አከባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከጉዞ ሰነድና ፓስፖርት ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት ከተለያዩ ግዛቶች ከተውጣጡ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አመራሮች ጋር አካሂዷል።
በውይይቱም በጅዳ የኢፌዲሪ ቆንስል የሚሸፍናቸው ሰባት የተለያዩ ግዛቶች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ዜጎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።




በዚህ ወቅትም ዜጎች ከፓስፖርትና ህጋዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር በሚመለከት በጅዳ በኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራልና በኮሚኒቲ ተወካዮች አማካኝነት በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሯ ከዜጎቹ ጋር የነበረው ውይይት ያለውን ችግር በተጨባጭ ለመገንዘብ የረዳ መሆኑን በመጠቆም መንግስት ለዜጎች ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ የተነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋማቸው እየተገበረ ያለውን የሪፎርም ስራ አብራርተተዋል።
ከፓስፖርት እድሳት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከዚህ ቀደም ህጋዊ ሰነድ ኖሯቸው ላመለከቱ ዜጎች የእድሳት አገልግሎት መሰጠቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በቀጣይ የዜግነት ማጣራት ስራ በተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ለዚህም የኮሚዩኒቲ አመራር ህገወጥ ደላሎችን በማጋለጥ፣ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲስተናገዱ ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ ከተቋሙ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ከጉዞ ሰነድ ጋር በተያያዘ ያለ ችግርን ለመቅረፍ አሁን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ካለው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አቅርቦቱን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በዋና ዳይሬክተሯ የተመራው የልዑካን በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንሱል ጀነራል ከሆኑት ክቡር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል ጋር በመሆን ወደ አገራቸው ለመመለስ የተለዩ ዜጎችን በእስር ቤት በመገኘት መጎብኘትና ማነጋገር ችሏል።
