ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንገደኞች መረጃ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላትን ዝግጅት አጠናቃለች 

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንገደኞች ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላትን የህግ ማዕቀፍና የቴክኖሎጂ  ዝግጅት ማጠናቀቋን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ።ዋና ዳይሬክተሯ በኬኒያ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ የኢሚግሬሽን ዋና ሃላፊዎች ስብሰባ ላይ እየተካፈሉ ሲሆን በዚህም ከሰባት የምስራቅ አፍሪካ አገራት የተውጣጡ የዘርፉ ሀላፊዎችና ቴክኒካል ቡድን አስተባባሪዎች ተገኝተውበታል። 

መድረኩ በአቬሽንና ድንበር ቁጥጥር ዘርፍ የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን በዘርፉ ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑም ተጠቁሟል። 

ዘመናዊ የመንገደኞች መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂን በአሁን ሰዓት በዓለም ላይ 109 አገራት ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን በአፍሪካ ሩዋንዳ፣ደቡብ አፍሪካና ኬኒያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ተግባራዊ አድርገዋል።ኢትዮጵያም በቀጣይ ይህንን ዘመናዊና የአገር ደህንነትን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠር ትልቅ እገዛ ያለውን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ከሌሎች አገራት ጠቃሚ ልምድ የቀሰመችበት መድረክ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። 

የአለማቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አገራት ይህንን ስርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መስፍርት ያለው ሲሆን የስርዓቱ ተግባራዊነት የአገርን ደህንነት በላቀ መልኩ ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት