የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባቀረባቸው 3 ረቂቅ አዋጆች እና 1 ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል። 

የመጀመሪያው የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን መሰረታዊ ከሆኑ መብቶች አንዱ የሆነውን የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር፣ የኢሚግሬሽን አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያዊንና ለውጭ አገር ዜጎች በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና መስጠት እንዲቻል፣ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የተሟላ የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ሁለተኛው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን በድጋሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ስርዓት የሰፈነበት እንዲሆን፣ የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት በሚገባ የሚያስጠብቅ ስልጣንና አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ 

ሶስተኛው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ማድረግ፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረታዊ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና ለማስከበር ሁሉን አቀፍ የምዝገባ ስርዓት መዘርጋት የሚገባ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ 

ምክር ቤቱም በቀረቡት 3 ረቂቅ አዋጆች ላይ በሰፊው ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

አራተኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ 

ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ መሸፈን የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡