የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ 


የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ በሲስተም ዝርጋታ፣ በሰው ኃይል  ስልጠና እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ሁለቱ ተቋማት አብሮ ለመስራት ያስችላቸዋል፡፡  በዚህም የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እገዛ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተመላክቷል፡፡ የመግባቢያ ሰነዱን የኢሚግሬሽና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እና የኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር  ወርቁ ጋቸና (ኢንጅነር) ተፈራርመዋል፡፡  በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢንጅነር) ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ ለዜጎች የሚሰጠዉን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድርግ ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊዉን እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል ፡፡ የአገልግሎቱ  ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማታቸዉ እንዳስደሰታቸዉ በመግለጽ፤ ተቋማቸው የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ከኢንስቲትዩቱ ጋር መስራት አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡