የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡  

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ከኢመደአ ጋር በጋራ ለመስራት መስማማታቸው እንዳስደሰታቸዉ በመግለጽ፣ ተቋማቸው የሚሰጠውን አገልግሎት በማዘመን የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እና ተቋሙ በባህሪው የሚይዛቸው መረጃዎች ሚስጥራዊነት እና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከኢመደአ ጋር መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ወደፊት በርካታ ሥራዎችን በጋራና በትብብር እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡

በስምምነቱ ላይ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ባስተላለፉት መልዕክት ኢመደአ የኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መሠረተ-ልማት ደህንነት መጠበቅ ኃላፊነቱና ተልእኮው እንደመሆኑ መጠን ለመንግስት ቁልፍ ተቋማት የ24/7 የደህንነት ጥበቃ ከማድረግ ባሻገር ክልከላ ያለባቸውን ሶፍትዌሮችና ሀርድዌሮችን አበልጽጎ የማስታጠቅ ሥራን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን አያይዘውም ዛሬ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር የተደረገው ሥምምነት የኢ-ፓስፖርት ሥርዓትን ከዲዛይን ጀምሮ ደህንነትን መሰረት ያደረገ የሲስተም ግንባታ፣ የ24/7 የሳይበር ደህንነት ጥበቃ አገልግሎት፣ የሳይበር ደህንነት ኦዲት፣ አገልግሎቱ ያሉበትን የሳይበር ደህንነት ሥጋትና የተጋላጭነት ክፍተቶችን የመለየትና የመድፈን ስራዎችን በመስራት ተቋሙ የጀመረዉን በቴክኖሎጂ የመዘመን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ጠቁመዋል። 

በዚህ የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ኢመደአ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።