በጅቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመፍታት በተለየ መልኩ እንደሚሰራ ተገለፀ።
በጅቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር በተሻለ መልኩ ለመፍታትና የድንበር ኬላ ትብብርን ለማጠናከር በተለየ መልኩ እንደሚሰራ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገልጿል።
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በሆኑት ክብርት ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የልዑካን ቡድን በጅቡቲ የሚኖሩና ሀገሪቱን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ሰነድ አልባ የሆኑ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍና ከኬላ ቁጥጥር ላይ ያለ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ምክክር ከተለያዩ አካላት ጋር አድርጓል።
ልዑኩ በጅቡቲ ቆይታው በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የጅቡቲ ሀላፊና በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በዘርፉ ባሉ ችግሮች እና በሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙርያ ጠቃሚ ውይይት አካሂዷል።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በነበረ ምክክር፣ ከሰነድ አልባ ዜጎች፣ የፓስፖርት አቅርቦትና ከድንበር ኬላዎች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ሁኔታዎችን በሚመለከት ገለፃ ቀርቦለት ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ኢትዮጵያዊያን በአግባቡ በመለየትና ሰነዳቸውን በማጣራት የጉዞ ሰነድ እንዲዘጋጅላቸው በማድረግ ወደ አገር የማስመለስ ስራ ላይ ያለው ክፍተት እንዲስተካከል ማስቻልና ይህንንም ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።





በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጅቡቲ የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከዜግነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ስራዎች በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል። በድንበር አከባቢ የሚደረጉ ቁጥጥሮችም ጠበቅ ያሉና ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ሰላማዊት ዳዊት በምክክሩ የቀረበው ገለፃ በዘርፉ ያለውን ሁኔታውን በተሻለ መልኩ ለመገንዘብና የተሻለ መፍትሄ ለመስጠት የረዳ መሆኑን ገልፀዋል። ሰነድ አልባ ዜጎችን በተገቢው የመለየትና የጉዞ ሰነዶችን በወቅቱ እንዲደርሳቸው የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ከዜጎች ማጣራት ጋር እና ከድንበር ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስርዓቱን የማዘመንና ወቅቱን በሚመጥን አግባብ እንዲደራጅ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የጂቡቲ ሀላፊ ታኒያ ፓሲፊኮ በዓለም አስከፊ ሁኔታን እየተጋፈጡ ካሉ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ መሆናቸውን በመግለፅ ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ተቋማቸው
እያከናወነ ያለውን ጥረት ጠቅሰዋል።በቀጣይም ከፍልሰተኞች ሰነድና የማስመለስ ስራ ጋር በተያያዘ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ወ/ሮ ሰላማዊት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድርጅቱ እያከናወነ ላለው በጎ ተግባር ምስጋና በማቅረብ ቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የአለማቀፉ ድርጅት ድጋፍ እንዳይለይ ጠይቀዋል። በዋና ዳይሬክተሯ የተመራው ልዑክ በጅቡቲ ጊዚያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ ሲሆን በነፃ የንግድ ቀጠና እና ወደብ አከባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችንም ጎብኝቷል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
