የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመካፈል ለመጡ  ከ12ሺ በላይ እንግዶች ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት መሰጠቱ ተገለፀ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባኤና በ46ኛ የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ  12,271 እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠቱን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገልፀዋል። 

ዋና ዳይሬክተሯ ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በተቋሙ በኩል የተሰራውን ስራ በማስመልከት በሰጡት ሀሳብ ተቋሙ ለጉባኤ  መሳካት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ሲሰሩ የነበረውን ስራዎች በማስታወስ ለጉባኤው ስኬት በልዩ ትኩረት መሰራቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የእንግዶችን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ባለሙያዎችን በመለየት በVIP እና መደበኛ ተርሚናሎች በማሰማራትና የቴክኖሎጂ አቅምን ከፍ በማድረግ እንዲሁም የሰው ሀይሉን ከእንግዶች ቁጥር ጋር የተጣጣመ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ተቋማዊ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣቱን  ተናግረዋል። 

የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችም ልዩ ትኩረት በመስጠት አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው ቦታዎች ላይ  ቅኝትና ምልከታ በማድረግ የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ እንከን የለሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ እንዲሆን የቅርብ ክትትል ማድረጉን አብራርተዋል። 

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከጉባኤው የዝግጅት ኮሚቴ ጋር በመናበብና በመቀናጀት ኢትዮጵያ ጉባኤውን በስኬት እንድታጠናቅቅ የተጣለበት ተቋማዊ ሃላፊነት በብቃት መወጣቱንም ወ/ሮ ሰላማዊት ገልፀዋል ። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት