አዲስ አበባ፡ መስከረም 3/2017 ዓ.ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትን ጨምሮ የተቋሙ አመራሮች ከቶፓን ኩባንያ እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር የፓስፓርት ምርትና አቅርቦት መጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ በፓስፓርት አገልግሎት የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለትምህርት፥ ለስራ፥ ለቱሪዝም እና መሰል ጉዳዮች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ጋር ተያይዞ የፓስፓርት ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ተቋሙ ይህን የህብረተሰቡን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የፓስፖርት ምርትና አቅርቦትን ከፍ ለማድረግ ከቶፓን ኩፓንያ እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ሰላማዊት አያይዘውም ተቋሙ ከተደራሽነት አንፃር ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች በሚገኙ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ያለውን አገልግሎት እስከ ምሽት የሚቆይ አገልግሎት መጀመሩን፥የሰው ሀይል እና ሌሎች ግብአቶች መሟላታቸውንም ገልፀዋል። በአንድ ማእከል አገልግሎት መሶብ ተቋሙ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም ወይዘሮ ሰላማዊት ተቋሙ “የተገልጋዮችን ደስታ እና የደንበኞቹን እርካታ” የስራ ሚዛን ፥ የስኬት መስፈሪያ አድርጎ ዘመናዊ እና ፈጣን አገልግሎት መስጠቱን እንደሚቀጥል እና ለተሻለ ተቋማዊ ለውጥ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
