የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ የሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ ቀንን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገለፀ ። 

አዲስ አበባ፡ መስከረም 09 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም የሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ ቀን በዓልን ለማክበር ባለዉ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የሲቪል ምዝገባ ስርዓት በሃገሪቱ የሚገኙ ዜጎችን ከልደት እስከ ህልፈተ ህይወት የሚከሰቱ ክስተቶችን በመመዝገብና በማከማቸት በዋነኛነት ለህግ፣ለአስተዳደርና ለስታትስቲክስ ፍጆታ ማዋል መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም ይህን የሲቪል ምዝገባ ስርአት በመምራት፥ በማስተባበር እና በመደገፍ  ተቋሙ ተልኮውን በሚገባ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የሲቪል ምዝገባ ስርዓት በአስተማማኝ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን እና የወሳኝ ኩነቶችን ማስመዝገብ ያለውን ጠቀሜታ በማስገንዘብ የማህበረሰብ ንቅናቄ እና መነቃቃት  ለመፍጠር በማሰብ ቀኑ እንደሚከበርም ነዉ የተገለጸዉ።ከዚህም ባለፈ የፓሊሲ ቁርጠኝነት እንዲኖርና ከፌድራል እስከ ወረዳ የሚገኙ የምዝገባ ኤጀንሲዎችና ሌሎች መዝጋቢዎች ተሞክሮ ለመለዋወጥ እና ቅርርብ ለመፍጠር ቀኑ መከበሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አለውም ተብሏል።

በጅማ ከተማ በሚከበረው 8ኛው የሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ ቀን የልደት፥ ጋብቻ፥ ፍቺ፥ ሞት እና ሌሎች የሲቪል ምዝገባ ስራዎች ፋይዳ የተመለከተ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል። በተጨማሪም የሲቪል ምዝገባን ዲጅታላይዝ በማድረግ የተሻለ ተሞክሮ ባላቸው የምዝገባ ጣቢያዎች ጉብኝት በማካሄድ ክልሎች ልምድ እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133