የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን በዲጂታላይዜሽን አሰራር በመታገዝ የምዝገባ ስርዓቱን ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡

አዳማ፡ መስከረም 09 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ የስልጠና፣ የድጋፍ፣ ክትትልና ግምገማ መነሻ ሰነዶች ግብአት ለመሰብሰብ እንዲሁም ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚደረገውን የሲስተም ማልማት ተግባር ያለበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ጌታቸው ሰነዶቹ ተገቢውን ግብአት አግኝተው ወደ ተግባር ሲገባ  የሲቪልና ቤተሰብ  ምዝገባው ዘመናዊ አሰራር እንዲከተልና አገልግሎቱን ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡ ሲስተሙ ሲጠናቀቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ከወረቀት ስራ በማላቀቅ ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታላይዜሽን አሰራር የሚያሸጋግር መሆኑንም ነዉ የገለፁት ዳይሬክተሩ። 

የስልጠና፣ የድጋፍ፣ ክትትልና ግምገማ መነሻ ሰነዶች ለተለያዩ የዘርፉ አመራርና መዝጋቢ አካላት በሚመጥን መልኩ እንደተዘጋጀ የገለፁት የሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታጁ መሀመድ በበኩላቸዉ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሞክሮ በመጠቀም እየዳበረ መሆኑን ተናግረዋል።  ሰነዶቹ ሲያልቁ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅን ዓላማ በሚያሳካ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የስልጠና እና የድጋፍ፣ክትትልና ግምገማ ሰነዶቹ ላይ ግብአት የመስጠት እንዲሁም ምዝገባውን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ ያለዉን አዲስ ሲስተም የደረሰበት ደረጃ የገመገመው ይህ መድረክ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133