የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ያሳየዉን የላቀ አፈጻጸም በቀጣይ አመትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።

አዲስ አበባ፡ ሀምሌ 02/2017 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅትን በተቋሙ ማኔጅመንት ደረጃ የገመገመበት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ  ተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም በሪፎርም ሥራዎች አፈፃፀም የታዩትን ጠንካራ ጎኖችና የገጠሙትን ተግዳሮቶች በጥልቀት ተዳሰዋል።

በተጨማሪም በበጀት አመቱ የታዩ አመርቂ አፈፃፀሞች የተበረታቱ ሲሆን፣ የተለዩ ክፍተቶችን ደግሞ በቀጣዩ 2018 በጀት ዓመት ለማሻሻል በእቅድ እንዲካተቱ ተደርጓል።

በውይይቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ያሳየዉን የላቀ አፈጻጸም በቀጣይ አመትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የገለፁ ሲሆን አክለውም ባለፈው በጀት አመት ተደራሽ ማድረግ ላይ በርካታ ስራዎች የሰራን ሲሆን በ2018 በጀት አመት ግን አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የደንበኞችን እርካታም እየለካን የምንሰራበት አመት ይሆናል ብለዋል። 

በተጨማሪም ባለፈው አመት ብዙ ስራዎችን በአንድ ጊዜ ጀምረን ብዙዎቸን መጨረስ መቻላችን  እና በብዙ ፈተናዎች ተስፋ ሳትቆርጡ ይህንን ውጤት ማምጣታችን የሁሉም ውጤት ነውና ልትመሰገኑ ይገባል ያሉ ሲሆን በቀጣይ በጀት አመት 24/7 በመስራት ዕቅዳችንን ማሳካት ይኖርብናል ብለዋል።

በመጨረሻም የ2018 በጀት አመት ዕቅድ የቀረበ ሲሆን የተለያዮ ግብአት ተሰጦበት ዕቅዱ ፀድቋል። በቀጣይም ከዋና ዳይሬክተር ጀምሮ ሁሉም ዘርፎች ከሚመለከታቸው የስራ ክፍል ጋር የፊርማ ስነ ስርዓት በማድረግ እቅዱ እስከታች ካስኬድ እንዲደረግ አቅጣጫ ተሰጥቷል።