ከሲቪል ምዝገባ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት  የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የክብር መዝገብ ሹሞች በሲቪል ምዝገባ መሰረታዊ ጉዳዮች እና በመረጃ ምንነት፣ ጥራትና አጠባበቅ ላይ ስልጠና ሰጠ።

ስልጠናው በመቐለ ከተማ የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዓላማም የክብር መዝገብ ሹሞች በምዝገባ ሂደት የሚፈጥሯቸው የአመዘጋገብ ክፍተቶችን በማሳየት በተቻለ ፍጥነት የሚስተካከሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እና ከሲቪል ምዝገባ የሚገኘው መረጃ ጥራት ያለው እንዲሆንና ለሚፈለገው አላማ እንዲውል የሚያስችል ግንዛቤ ለመፈጠር እንደሆነ ተገልፆል፡፡

አሁን ላይ ያለው ምዝገባ እንደ አገር ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ጥራት ያላቸው መረጃዎችን ከማመንጨት አንጻር ውስንነት እንዳለው የተገለፀ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በማንዋል እየተካሄደ የሚገኘው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ምዝገባ ስርዓት  በመሸጋገር ላይ  እንደሆነ ተነግሯል። 

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል የስታትስቲክስና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ኃላፊ ዶ/ር ገብረሀዋርያ ገ/እግዚአብሔር  የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በተከታታይ ጊዜ ለሚያደርገው ድጋፍ አመስግነው ሰልጣኞች የተሰጠውን ስልጠና ወደተግባር በመቀየር ጥራት ያለው መረጃ በመላክ በጊዜ ለሚፈለገው አላማ እንዲውል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።