አሜሪካን በድንበር ቁጥጥር ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ገለፀች።

አዲስ አበባ፡ 29/09/2017 ዓ.ም

አሜሪካን በድንበር ቁጥጥር ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር ማዕቀፍ ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ገልፃለች።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በአሜሪካን የአሸባሪዎች መለያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ግላሺን የተመራ የልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በውይይታቸው ወቅትም  ኢትዮጵያ በብሔራዊ ደህንነት አጠባበቅ ዙሪያ ያላትን አሰራርና ለዘርፉ የምትሰጠውን ልዩ ትኩረት በሚመለከት ለቡድኑ አባላት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን መቀያየር አሸባሪዎችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ያላትን የአየርና የየብስ ድንበሮች  ቁጥጥር የበለጠ ለማዘመን አጋዥ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ሀይል እየተጠቀመች ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት እየዘረጋች መሆኗን ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።

ሚስተር ሚካኤል ግላሺን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በድንበርና አየር ቁጥጥር ተግባራት እያከናወነችው ያለውስራ የሚደነቅ መሆኑን የገለፁ ሲሆን  አሜሪካም በዘርፉ ያላትን መልካም ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡ 

በውይይቱ የተሳተፉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በበኩላቸው ተቋሙ በአየርና የብስ ድንበር እንዲሁም  በውጭ ዜጎች ቁጥጥር  ላይ እያከናወነ ያለውን ጠንካራ ስራ  በመግለፅ በዚህ ዘርፍ መልካም ተሞክሮ ካላቸው እንደ አሜሪካን የመሳሰሉት አገራት  ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ አካላት በተለይ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይበልጥ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ ከማድረግ አኳያ በአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ አንፃር ይበልጥ በጋራ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት