አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በመረጃ ልውውጥ እና በአቅም ግንባታ ስራ በጋራ አብረው ለመስራት ተስማምተዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት አገልግሎቱ ሪፎርም ላይ መሆኑንና እገልግሎቱን የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህም በተለይ ከመረጃ ልውውጥ፣ ከስልጠና እና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በአገልግሎቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ስምምነቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እያደረገ ላለው ድጋፍና እገዛም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸዉ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር የተፈራረመው የስምምነት ሰነድ ሁለቱ ተቋማት በለውጡ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂና ሌሎች አቅሞችን አደራጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ተቀራርበው ከመስራት ይልቅ መገፋፋት የሚታይባቸው እንደነበር ያስታወሱት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ ከለዉጡ በኋላ ግን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በማድረግ፣ ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ አቅሞችን በማስተባበር፣ ሰላምና ደህንነትን በማስከበር ረገድ ትላልቅ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርመራ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የኢሚግሬሽን ኦፊሰሮች በኢትየጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ የትምህርትና የስልጠና ዕድል እንደሚያገኙ በስምምነቱ ላይ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልጸዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
