ቋሚ ኮሚቴው፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን የስራ አፈፃጸም ገመገመ 

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ9 ወራት የስራ አፈጻጸምን  ገመገመ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴን የመስክ ምልከታን ጨምሮ ሲከታተል እንደነበረና የዕቅድ አፈጻፀሙንም መገምገሙን ገልፀዋል።

በዚህ ውይይትም በተቋሙ የስራ አፈፃጸም ዙሪያ የሚነሱ ግልጽነት የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ቀርበው ማብራሪያ እንደሚሰጥባቸውም ጠቁመዋል።

የተቋሙ የ9 ወራት የስራ አፈጻፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በተሰራው የሪፎርም ስራ አሰራርን የጣሱ ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂ የማድረግ፣ ለበርካታ ዜጎች አዲስ ፓስፖርት የመስጠትና የማደስ፣ ውዝፍ አገልግሎቶችን የማጠናቀቅ ፣ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን ወደህጋዊ መንገድ የማስገባት፣ አሰራሮችን ለማዘመን ከተለያዮ ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን የማልማት እና ስለ ተቋሙ የግንዛቤና የገጽታ ግንባታ ስራዎች በዋናነት መሰራታቸው ተብራርተዋል።

በሌላ በኩል የሲቪል ምዝገባን በተጠናከረ መንገድ ለማካሄድ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የጸጥታ ችግር መኖር፣ የተቋሙን ተልዕኮ ሊሸከም የሚችል አደረጃጀትና የሰው ሀይል ያለመሟላት እና አገልግሎቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያለመዘመን በሪፖርቱ በእጥረት ከተነሱት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

የተቋሙን የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻፀምን አስመልክቶ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጁ ጥያቄዎች በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑ የምክር ቤት አባላት እና ባለድርሻ አካላት የቀረቡ ሲሆን፤  የተቋሙ  አመራሮች በቀረበው ጥያቄ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በተጨማሪ ቋሚ ኮሚቴው በ9 ወር ሪፖርቱ እና በመስክ ምልከታ ያዮትን ግብረ መልስ በመስጠት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በማመላከት ውይይቱ ተጠናቋል።