የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት ወደ ተቋሙ በቅርብ ጊዜ የተቀላቀሉ አዲስ ሰራተኞች የተቋሙ ስራና ኃላፊነት በተለይ በሰነዶች አሰጣጥ፣ የውጭ ዜጎች አገልግሎት፣ የውጭ ዜጎች ምዝገባና ቁጥጥር፣ የአየርና የብስ ኬላዎች አገልግሎትና ቁጥጥር እንዲሁም ደንበኞች አያያዝን በተመለከተ ከግንቦት 24 እስከ ግንቦት 26/ 2016 ዓ.ም የሁለት ቀን ስልጠና በአዳማ ከተማ ሰጥቷል፡፡






በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው ለአዲስ ሰራተኞች መልዕክት ያስተላለፉት የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አዱኛ፣ ተቋሙ ከያዘው ሪፎርም ቁልፍ ተግባራት አንዱ የሰው ሃብት ልማት ማጠናከር በመሆኑ አዳዲስ ከሚቀጠሩ ሰራተኞች በተጨማሪ የነባር ሰራተኞች አቅም ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አክለውም የሰው ሃብት በእውቀትና ክህሎት ማበልፀግ ብቻውን በቂ እንዳልሆነና የተቋሙ መሰረታዊ እሴቶች የሆኑ በታማኝነትና በአገልጋይነት ስሜት በተቋሙ የተጀመረው የሪፎርም ሂደት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት ስልጠናና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኑት አቶ ከተማ አለሙ በበኩላቸው በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት ላይ የሚነሱ የደንበኞች አያያዝ ቅሬታዎች ለመፍታት በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰው ሰልጣኞች በስልጠና ያገኙት አቅም ወደ ተግባር በመቀየር የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተወፅኦ እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መሰረታዊ አገልግሎቶችና በደንበኞች አያያዝ አተኩረው የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ሰልጣኞችም ስለ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት መሰረታዊ እውቀት እንደጨበጡ ገልፀዋል፡፡
