በኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ የተመራ ቡድን የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

አዲስ አበባ: ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ  የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ሀብት ልማት እንዲሁም ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ላይ መሰረት ያደረጉ የሪፎርም ስራዎች መስራቱ ለህብረተሰቡ  የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

ኤጀንሲው የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት አቶ ቢቂላ ተቋማቸው የጀመረውን የቤተሰብ ምዝገባ ከነዋሪነት ምዝገባ ጋር በማጣጣም መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡  አቶ ቢቂላ አክለውም ኤጀንሲው ለክልሎች  አርአያ የሚሆን ስራ ሰርቷል ያሉ ሲሆን በቀጣይ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለኤጀንሲው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ኤጀንሲው አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ዘመናዊ እና ደህንነቱ የጠበቀ የመረጃ አያያዝና አስተዳደር ስርአት እንዲኖር አዳዲስ አሰራሮች መዘርጋቱን ገልፀው ለአብነትም ኤጀንሲው አዲስ የመረጃ ማዕከል አቋቁሟል ብለዋል። አክለውም ወረቀት አልባ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን እና የመኪና ስምሪት መቆጣጠሪያ ሲስተሞች በኤጀንሲው አማካኝነት መልማት መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡

በአደረጃጀት በኩል የህግ እና የህትመት ዳይሬክቶሬቶችን ማቋቋም፣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መክፈት፣ በ143 የጤና ተቋማት የወቅታዊ ኩነት ምዝገባ ማከናወን እንዲሁም በ11 የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና ሸሪዓ ፍርድ ቤት መዋቅር በመዘርጋት የኩነት ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

በውይይቱ መጨረሻም በኤጀንሲው እጥር ግቢ ቴክኖሎጂ መሰረት አድርገው እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ጨምሮ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት፣በሸሪዓ ፍርድ ቤት እና በሚኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎች ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133