የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አቅም ለሌላቸው አንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ  ድጋፍ አደረገ። 

አዲስ አበባ:- ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም

ተቋሙ ድጋፉን ያደረገው በአዲስ አበባ  ቂርቆስ ክፍለ ከተማ  ለሚገኙ አንድ ሺህ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች  ነው። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት  ተቋሙ ከተሰማራበት ሃገራዊ ተልዕኮ ጎን ለጎን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ላይ ነው ብለዋል። ለአብነትም  በችግኝ ተከላ፥ ለአቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም  በደም ልገሳ  በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

”በትምርት ቁሳቁስ እጥረት አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ መቅረት የለበትም” በሚል መርህ ከ 4 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የቦርሳ፣  የደብተር፣ እሰኪሪብቶ እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሯ በቀጣይም ይህን የበጎ አድራጎት ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ምስክር ነጋሽ በበኩላቸዉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ውጤታማ ተቋማዊ ሪፎርም በማካሄድ የተቋም ግንባታን ለሌሎች ተቋማት እያሳየ መሆኑን  ጠቅሰው ለነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናት ያደረገዉ ድጋፍም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን እንደ አርእያ በመውሰድ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ሊሳተፉና  ማህበራዊ ሃላፊነታቸዉን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡