በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጪ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ የስራ ጉብኝትና ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አግልግሎት የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ እያካሄደ ያለውን የሪፎርም ስራ ለቋሚ ኮሚቴዎቹ ያብራሩ ሲሆን ተቋሙ ከ2015 ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት፤ የሰው ሀይልን ማብቃት እንዲሁም ጥናት ላይ መሰረት ያደረገ አሰራር መዘርጋት ላይ ትኩረት ያደረገ 11 የሪፎርም አጀንዳዎች ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ደንበኞች ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በኦንላይን የታገዘ አገልግሎት በመስጠት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች አዳዲስ ቅርንጫፎችን የማስፋፋት ስራ መሰራቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ በክህሎት እና በትምህርት ብቁ የሆነ ተጨማሪ የሰው ሃይል በመጨመር እና የስራ ሰአቱን ምሽትን ጨምሮ በቦሌ በአራት ፈረቃ በፓስፖርት አገልግሎት ሁለት ፈረቃ አድርጎ በመስራት የተቋሙን አግልግሎት ለዜጎች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የዜግነት ዘርፍ ም/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቄላ መዝገቡ በበኩላቸው ተቋሙ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት እና ቅርንጫፎችን ወደ 28 በማሳደግ ዜጎች በአቅራቢያቸው አግልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ከለውጡ በፊት 2010 ላይ 70ሺ ብቻ የነበረው አመታዊ የፓስፓርት ተደራሽነት ባለፈው 2016 አመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከፍ ማለቱ በተደራሽነት የተሰራ ሌላው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል ፡፡
የኢሚግሬሽና ዜግነት አግልግሎት የኢሚግሬሽን ዘርፍ ም/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ ከአገልግሎት ተደራሽነት በተጨማሪ የውጭ ዜጎችን እና የድንበር ቁጥጥር ስራ በማጠናከር የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት ለመጠበቅ እየተሰራ ያለዉን ስራ ለቋሚ ኮሚቴዎቹ አብራርተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴዎቹም በ2015 እና 2016 ዓ.ም የተነሱ የኦዲት ግኝቶች በርካታ ማስተካከያ ተደርጎባቸው ማየታችን የሚያበረታታ ነው ያሉ ሲሆን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሀገርን ጥቅም እና ሉአላዊነት መሰረት ያደረገ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኑን እና የዜጎችን መብት በሚጠብቅ መልኩ አዳዲስ አሰራሮችን እና መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን አድንቀዋል።
በመጨረሻም ተቋሙ የሀገሪቱን ገፅታ በጠበቀ መልኩ ለውጪ ዜጎች የሚሰጠው ፈጣን አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው ተቋሙን የማዘመን፣ ተደራሽነትን የማሳደግ፣ የሰላም እና ደህንነት ጥበቃ ላይ ያለው ለውጥም ሊጠናከር እንደሚገባ እና ቋሚ ኮሚቴው ለተቋሙ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
