የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት የተሻለ አገልግሎት ለዜጎች በመስጠት በሀገር እድገት ላይ የራሱን አሻራ ለመጣል እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

አዲስ አበባ: ሐምሌ 16/2017

ተቋሙ በ2018 ዓ.ም አጠቃላይ ሀገራዊ እቅድ እንዲሁም በተቋሙ የ 2018 ዓ.ም እቅድ ዙሪያ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በ2017 የበጀት አመት እንደ ሀገር በተመዘገበው ሁለንተናዊ እድገት ላይ ተቋሙ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን ጠቅሰዋል፡፡ 

የሀገሪቱን አጠቃላይ ገቢ በማሳደግ፣ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ፣ የየብስ ድንበር እና የአየር ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ ለውጦች ላይ ተቋሙ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም የእቅድ ዘመንም ተቋሙ ከሀገራዊ እቅዱ ጋር ተመጋጋቢ እቅድ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን የገለፁት  ም/ዋና ዳይሬክተሩ ተቋሙ  ዜጋ ተኮር አገልግሎት በመስጠት በሀገር ግንባታ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማበርከት ስራውን ይቀጥላል ብለዋል። አያይዘውም የተቋሙ ሰራተኞች በብቃት፣ በንቃት እንዲሁም ኃላፊነትና ብሄራዊ ስሜትን ተላብሰው  እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የኢምግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት የእቅድና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሳይ አበበ በበኩላቸው ተቋሙ በ2018 ዓ.ም 1 ነጥብ 5 ሚልዮን አስቸኳይ ፓስፖርትን ጨምሮ በአጠቃላይ  4 ሚልዮን ፓስፖርት ለዜጎች ለመስጠት መታቀዱን ገልፀው 

የአመራር እና የሰራተኛ አቅምን  ማሳደግ እንዲሁም አሰራሮችን ህጋዊ ስርአት የተከተሉ እና በቴክኖሎጂ የተደገፋ እንዲሆኑ ማድረግ የ2018 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል።

አክለውም የፓስፓርት ፈላጊውን ቁጥር ጥናት በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከፈቱ አዳዲስ ቅርንጫፎች በቴክኖሎጂ እና በሰው ሀይል የማጠናከር ስራ  በ2018 ዓ.ም በጀት አመትም ይቀጥላል ያሉ ሲሆን የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ስራዎችን ዲጅታላይዝ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም በውይይቱ ላይ ገልፀዋል።

የተቋሙ ሰራተኞችም ተቋሙ ምቹና ዘመናዊ አግልግሎት ለመስጠት እየሰራ ባለው የሪፎርም ስራ እና ባለፉት ሁለት አመታት ያስመዘገበው ለውጥ አካል በመሆናቸው ደስተኞች መሆናቸውን በመግለፅ በቀጣይ የተቋሙን እቅድ እውን እንዲሆን  የተቋሙን ህጋዊ አሰራር በተከተለ መልኩ በታማኝነት እና በቅንነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።