የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በቀጣይ ተቋሙን በተለያዩ ሙያዎች የሚያገለግሉ አዳዲስ ባለሙያዎችን ከብሔራዊ ደህንነት ዮኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በማሰልጠን አስመርቋል። ባለሙያዎቹ የተቋሙን ተልዕኮ በብቃት ለማስፈፀም እንዲያግዙ ለማስቻል የተቀመጠውን መስፈርት በማሟላት በሴኪውሪቲ እና ኢንተለጀንስ፣ በዲኘሎማቲክ ፕሮቶኮል፣ በቱሪዝም እና በስነ-ምግባር ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው።




በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ላይ መሆኑን በማስታወስ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትና ለተገልጋዩ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ሀይል ልማት ላይ በተለየ ትኩረት ለመስራት በተቋሙ የተያዘው የሪፎርም አካል መሆኑን አስረድተዋል።
ሰልጣኞቹም አለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉንና የወሰዱትን ስልጠና ወደ ተግባራዊ ስራ በመቀየር ተገልጋዩን በተሻለ መልኩ እንዲያገለግሉ አደራዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ተቋሙ በቀጣይም የሚስተዋሉበትን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ለነባር እና አዳዲስ ሰራተኞች በተግባር የተደገፈ እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚረዳ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ አክለው ገልፀዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
