የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ውይይት አደረገ ። 

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በ29ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራቸው ሶስት ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገለፃ አድርጓል፡፡ ማብራሪያ እና ውይይት የተደረገባቸው ረቂቅ አዋጆች፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/9 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ 19/2016 እንዲሁም የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ 20/2016 ናቸው፡፡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በነዚህ ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር የአንድ ቀን ውይይት አድርጓል። 

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በተቋሙ የሚስተዋሉትን በርካታ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋማዊ ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ ተቋሙን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ የሰው ኃይል ማልማትና ማደራጀት፣ ብሎም ህግና አሰራሮችን ማሻሻል የሪፎርሙ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

እነዚህና ሌሎች የሪፎርም ተግባራትን ለማከናወንም የተቋሙ ህግና አሰራር ማሻሻል ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል።  ተቋሙ የዓለም አቀፍ የሲቪል አቬሽን ድርጅት (ICOA) መስፈርትን የሚያሟላ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ የድንበር አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት፣ ሀገሪቱን የተጠበቀችና የተከበረች ለማድረግ የሚያስችል ህግ ማፅደቅ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል። አክለውም፣ ረቂቅ ህጉ ከመረቀቁ በፊት በተቋሙ የሚስተዋሉትን የህግና የአሰራር ክፍተቶች ለመለየት ሰፊ ጥናት መደረጉንና የበርካታ ሀገራት ልምዶችም ታሳቢ መደረጋቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም የተከበረው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ የአዋጁን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቂ ውይይት በማድረግ ረቂቅ ህጉ በቅርቡ ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል። 

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ  እፀገነት መንግስቱ በበኩላቸው በሀገራችን የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ የመንግስት ተቋማት በሪፎርም ሂደት ላይ እንደሚገኙና ከዚህ በፊት የደረሰባቸው የህግ ስብራት ለመጠገን ህጎቻቸውንና አሰራራቸውን በማሻሻል ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንን ስብራት ለመጠገን በአገራችን የተጀመረውን የሪፎርም ሂደት ለመደገፍ በርካታ አዳዲስ ህጎችና ማሻሻያ ህጎች እንዳፀደቀ ገልፀዋል። አክለውም፣ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ የቀረቡ ሪቂቅ ህጎችን በዝርዝር በመመርመር ጥራት ያለው ህግ ሆነው እንዲፀድቁ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133