የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲዎች እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቅንጅታዊ ሥራዎች ዙሪያ ምክክር አደረገ።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወልዴ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን፣ ተግባር እና ሐላፊነት መካከል የወሳኝ ኩነት እና የቤተሰብ ምዝገባ ስራዎችን መምራት፣ ማስተባበር እና መደገፍ እንደሚገኝበት ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ እና ዋነኛው ተግባር ይህ መሆኑን ያስረዱት ሐላፊው፣ የምዝገባ ስርአቱን ለማጠናከር ከሚያካሒዳቸው አሰራሮችን የማዘመንና ተደራሽ የማድረግ ተግባራት በተጨማሪ፣ በጉዳዩ ዙርያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን የማጠናከር ተግባርም ያከናውናል ብለዋል፡፡ 

ከነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከል የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በ2010 ዓ.ም በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አተገባበር ስርአት ዙሪያ ያላቸውን ተግባር እና ኃላፊነት መሰረት ባደረገ መልኩ አብረው ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረሙን ገልፀዋል፡፡ 

ሁለቱም ፈራሚ ተቋማት በስምምነታቸው መሰረት ወደ ስራ ገብተው፣ በየደረጃው የሚገኙ የክልል እና የከተማ አስተዳደር መዝጋቢ አካላት እና የትምህርት መዋቅሮች የተሰጣቸውን ተግባር እና ሃላፊነት እንዲወጡ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ተስፋዬ አክለውም፣ ባለፉት ዓመታት የልደት እና የጉዲፈቻ ምዝገባ አፈጻጸምን ለማሻሻል በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ሴክተሮች ጋር በመተባር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰው፣ አሁንም በቀጠለው ይኸው ስራ በተለይም የልደት ምዝገባን ከማጠናከር አንጻር ህጻናት እንዲመዘገቡ እና የልደት ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ይህ እድል፣ በምስክር ወረቀት አማካኝነት የሚሰጡ የተለያዩ ማህበራዊ፣ የፍትህ እና የኢኮኖሚ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማስቻሉንም ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ አሰራሩን በማጠናከር፣ የህጻናትን መብት ለማስከበር እና ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

በመጨረሻም፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርአቱን በማጠናከር ረገድ ሁለቱ ተቋማት ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ ቅንጅታዊ ስራዎችን በጋራ አጠናክሮ በማስቀጠል እና የእቅዳቸው አካል በማድረግ በእቅድ ደረጃ የሚቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ 

የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እና የትምህርት ሚኒስቴር የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ በስልጠና እና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከተማ አለሙ አቅራቢነት ወይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ቀጥሎም የክልልና ከተማ መስተዳደር ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲዎች ከክልል ካሉ የትምህርት ቢሮዎች ጋር ያሉዋቸው ቅንጅታዊ አሠራሮች ታይተዋል፡፡ የስራዎቻቸውም ጠንካራና ደካማ ጎኖች ወደ መድረክ ቀርበው ሰፊ ወይይት ተደርጎባቸዋል። በመጨረሻም በተቋሙ እቅድ ዝግጅት ድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ቀርቦ በተሳታፊዎች ወይይት ተደርጎበት የውይይት መድረኩ ተጠናቋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133