አዲስ አበባ: ነሐሴ 06/ 2017 ዓ. ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በአገር ውስጥ እያካሄደ ያለውን የሪፎርም ስራ በውጭ አገር በሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በሚሰጣቸው የፓስፖርት፣ ቪዛ፣ ሊሴ ፓሴ እና ሌሎች አገልግሎቶች ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገለጸዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በተለያዩ ሀገራት ለሚሰሩ የቆንስላ ሰራተኞች በተሻሻሉ የኢሚግሬሽን የህግ ማዕቀፎችና ሌሎች ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረዉን ስልጠና አጠናቋል።
በስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማዘመን፥ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ፥ የሰው ሃይል አቅምን ማሳደግ ጨምሮ ሌሎች ውጤታማ የሪፎርም ስራዎችን ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ተቋሙ በውጭ ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይም በመተግበር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም እነዚህ የሪፎርም ስራዎች የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም እና ብሄራዊ ደህንነት በጠበቀ መልኩ በትኩረት ሊሰራባቸዉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎችን እርካታ እዉን በሚያደርግ መልኩ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ መሆን እንዳለበትም ነዉ ወ/ሮ ሰላማዊት ያሳሰቡት።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች የሪፎርም ስራ ከተጀመረበት 2016 ዓ.ም ወዲህ መሻሻሉን እና በውጪ ያለው አገልግሎት ፈላጊ ማህበረሰብ እርካታ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በቀጣይም በሚሰሩበት ቦታ የዜጎችን መብት እና የሀገሪቱን ገፅታ በጠበቀ መልኩ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ተቋሙ እያካሄደ ባለው የሪፎርም ትግበራ ላይ የበኩላችውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
ስልጠናው በተሻሻሉ የኢሚግሬሽን የህግ ማዕቀፎች ፤ በጉዞ ሰነድ አይነቶች እና ቅድመ ሁኔታዎች ፥ ኢ-ፓስፓርት እና በትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ አተገባበር፥ በቆንስላ በሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ሳምንት ሲሰጥ ቆይቷል ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
