አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም
ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ከክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ጋር በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በትብብር አብሮ መስራት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ በኦፕሬሽን፣ በድንበር ቁጥጥር፣ መረጃን ለመለዋወጥ እና በተለያዩ ሀገራችን አካባቢዎች ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሠራተኞች በኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል የሕህምና አገልግሎት ማግኘት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከዋና ዳይሬክተሯ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሁለቱ ተቋማት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት የእርስ በርስ ግኑኙነትን በማጠናከር በትብብር አብሮ መስራት ያለባቸውን ጉዳዮች ተለይተው መቅረብ እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር የምንሰራቸው ሥራዎች በርካታ ናቸው ካሉ በኋላ የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በተጠና እና ስትራቴጂክ በሆነ መልኩ ከፍ ማድረግ ስላለብን ነው ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የመጣነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በሰው ኃይል ስልጠና ላይ፣ በኢሚግሬሽን ዕውቀት የተካኑ የፖሊስ ኃይል ምደባ ላይ፣ በየብስና በአየር ድንበር አገልግሎት እንዲሁም በተቋማት ጥበቃ እና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት በመዘርጋት ላይ በትብብር አብሮ ለመስራት በኢሚግሬሽን በኩል የተለዩ ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸው ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ሁለቱ ተቋማት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በቀጣይ በትብብር አብሮ በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ የመግባቢያ ሰነድ በቅርብ ቀናት ለመፈራረም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
