አዲስ አበባ ፡ ነሐሴ 1/2017 ዓ.ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጠው መደበኛ አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ በጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ ሲሆን በዛሬው እለት “ደሜ ለወገኔ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ጎተራ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት በጎ ፈቃደኛ አመራሮች እና ሠራተኞች 77 ዮኒት ደም የለገሱ መሆኑ ተገልፆል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ የደም ልገሳ ፕሮግራም ተቋሙ ከሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዉ በራስ ተነሳሽነት ደም መስጠት የህሊና እርካታ የሚሰጥና ደም በመስጠት ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት መታደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ተቋሙ በደም ልገሳና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይቀጥላል ብለዋል።
አቶ ሚካኤል አክለውም ደም ልገሳ የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚጠይቅ ታላቅ ሰብዓዊ አገልግሎት በመሆኑ ሁሉም ደም መስጠት የሚችል ሰዉ ሊያከናዉነዉ የሚገባ በጎ ተግባር መሆኑን ገልፀው በሁሉም ህብረተስብ እና ተቋማት ዘንድ ሊለመድ ይገባልም ብለዋል።
“ደሜ ለወገኔ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ደም በመለገስ የተሳተፉ አመራሮችና ሰራተኞች በተለያየ ምክንያትና አደጋ በደም እጦት የሚሞቱ ወገኖቻችንን ህይወት የማዳን ስራ ላይ በመሳተፋቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን ገልጸዉ በቀጣይም በዘላቂነት ደም ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከመደበኛ አገልግሎት በተጨማሪ በደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላ ፥ ለአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
