የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2018 በጀት አመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፓርት መስጠቱን ገለፀ።

አዲስ አበባ ፡ ሃምሌ 07 /2018 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2018 ዓ/ም በጀት አመት የእቅድ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን የሁሉም ዳይሬክቶሬቶች የበጀት አመቱ የስራ ክንውን ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ላይ እንደተገልጸዉ ተቋሙ በበጀት አመቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት ለዜጎች መሰጠት ተችሏል።

ከቪዛ አገልግሎት ጋር ተያይዞም ተቋሙ በበጀት አመቱ 1,046,286 ቪዛ ሰጥቷል። ከዚህም ባለፈ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያ 32,952 እንዲሁም ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ደግሞ 21,163 በመስጠት የተሳካ የእቅድ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ ተጠቅሷል።

ተቋሙ ከፓስፖርት፣ ቪዛ፣ ትዉልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከ42 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ስኬታማ ስራ መሰራቱም ነው የተገለፀው።

በአየር እና በየብስ ድንበር አለማቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ በጉዞ ሰነድ ለ7,225,691 ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል። ከሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከ6 ሚሊዮን በላይ ልድት እና ሌሎች ኩነቶችን መመዝገብ መቻሉም ተገልጿል።

ተቋሙ በበጀት አመቱ ህገወጥነትን ከመከላከል አንጻር 433 የውጭ ዜጎች እና 4,450 ኢትዮጵያውያን በሐሰተኛ ሰነድ የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽሙ ተይዘው ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን በሌላ በኩል 21 ግለሰቦች ደግሞ በህገ-ወጥ ድለላ ተጠያቂ ተደርገዋል። ከዚህም ባለፈ 174 ግለሰቦች ኦንላይን የአስቸኳይ ፓስፖርት በህገ-ወጥ መንገድ ሲሞሉ በመያዛቸዉ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንና ከዚሁ ጋር በተያያዘ 24 ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጉን ተገልጿል።

የፓስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከነባር 12 ቅርንጫፎች በተጨማሪ 11 የክልል ቅርንጫፎች እና በአዲስ አበባ ደረጃ ተጨማሪ ሁለት በአጠቃላይ በ23 የኢሚግሬሽን ቅርንጫፎች የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በመስጠት ስኬታማ ስራ በበጀት አመቱ ተከናዉኗል ተብሏል። በመሶብ የአንድ ማእከል ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት ተገልጋዮች በአቅራቢያቸዉ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ እና ተደራሽነትን ማስፍፋት ላይ ዉጤታም ስራዎች ተሰርተዋል ።

የኢሚግሬሽናና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ በ2018 ዓ.ም. በጀት አመት ካለፈዉ አመት ጋር ሲነጻጸር በሁሉም የአገልግሎትና የቁጥጥር ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጸዉ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተቋሙ ይጠቀምበት የነበረውን አሮጌ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በማቆም በዋና ቢሮና በሁሉም ቅርንጫፎች የኔትወርክ ዝርጋታ በማጠናቀቅ ወደ አዲስ የዲጅታል ሲስተም መሻገሩ ለስኬቱ ትልቅ አቅም መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም አሰራሮችን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የአመራሩና የባለሙያዉ ቁርጠኝነት፣ የሰው ኃይል ማሟላት እና በተከታታይ ስልጠና አቅም የማሳደግ ሥራዎች ለተመዘገበው ስኬታማ አፈጻጸም መሠረት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የ2018 ዓ.ም በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈ የቀጣዩን 2019 ዓ.ም በጀት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጎ እቅዱን አፅድቋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
ሁሉም የሚታወቅባት ኢትዮጵያ !
————————
ለበለጠ መረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ድህረ -ገፆችንን ይጎብኙ ይወዳጁን ……
Telegram: https://t.me/ICS_Ethiopia
Facebook: https://www.facebook.com/ICSEthiopia
Twitter: https://twitter.com/ics_ethiopia
TikTok: https://www.tiktok.com/@ics_ethiopia
LinkedIn: https://www.linkedin.com/company/icsethiopia
YouTube: https://www.youtube.com/@Ics_Ethiopia
Instagram: https://www.instagram.com/icsethiopia/