የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፋት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ፓስፓርት መስጠቱ ተገለፀ።

አዲስ አበባ ፡ ሚያዚያ 05 /2018 ዓ.ም

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2018 ዓ/ም 9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን የሁሉም ዳይሬክቶሬቶች የስራ ክንውን ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ተቋሙ በመደበኛና አስቸኳይ ፓስፖርት ፥ በቪዛ ፥ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ እና ሌሎች የይለፍና የጉዞ ሰነዶችን ለደንበኞች በመስጠት እንዲሁም በአየር እና የብስ ድንበር ቁጥጥር እና ሌሎች የተቋሙ አገልግሎቶች ባለፋት 9 ወራት ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጿል።

ተቋሙ ባለፋት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት ለዜጎች መሰጠት መቻሉ ተገልጿል።
ከቪዛ አገልግሎት ጋር ተያይዞም ተቋሙ በ9 ወራት ውስጥ 824,951 ቪዛ ሰጥቷል። ከዚህም ባለፈ 29,004 ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ በመስጠት የተሳካ የእቅድ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ ተጠቅሷል።

በአየር እና በየብስ ድንበር አለማቀፍ ስታንዳርዶችን በጠበቀ መልኩ በጉዞ ሰነድ ከ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱም ነው የተጠቀሰው።በህገ-ወጥ መንገድ የኦላይን የአስቸኳይ ፓስፖርት የሚሞሉ፣ በህገ ወጥ የድለላ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ እና የተቋሙን ስም በአሉታዊ መንገድ እንዲነሳ ያደረጉ ሀያ አንድ (21) ግለሰቦች ላይ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ በመተባበር በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ተገልጿል።

የፓስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከነባር 12 ቅርንጫፎች በተጨማሪ 11 የክልል ቅርንጫፎች እና በአዲስ አበባ ደረጃ ተጨማሪ ሁለት በጠቃላይ በ23 ቅርንጫፎች የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በመስጠት ስኬታማ ስራ በ9 ወራት ውስጥ ተከናዉኖአል ተብሏል።

የኢሚግሬሽናና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ በ2018 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ካለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጸዉ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተቋሙ ይጠቀምበት የነበረውን አሮጌ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በማቆም ወደ አዲስ የዲጅታል ሲስተም መሻገሩ ትልቅ አቅም መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

ወይዘሮ ሰላማዊት አያይዘውም አሰራሮች ዲጂታላይዝ ከመደረጋቸዉ ባለፈ የአመራሩ እና ሰራተኛዉ ቁርጠኛ መሆን እንዲሁም የሰዉ ሃይል የመሟላት እና አቅም የማሳደግ ስራዎች መሰራታቸው ስኬታማ አፈጻጸም እንዲኖር አስችሏልም ብለውል።

ተቋሙ ያለፋት 9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈ የመጪው የ3 ዓመታት(2019-2021 ዓ.ም) ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጎ እቅዱን አፅድቋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
ሁሉም የሚታወቅባት ኢትዮጵያ !
————————
ለበለጠ መረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ድህረ -ገፆችንን ይጎብኙ ይወዳጁን ……
Telegram: https://t.me/ICS_Ethiopia
Facebook: https://www.facebook.com/ICSEthiopia
Twitter: https://twitter.com/ics_ethiopia
TikTok: https://www.tiktok.com/@ics_ethiopia
LinkedIn: https://www.linkedin.com/company/icsethiopia
YouTube: https://www.youtube.com/@Ics_Ethiopia
Instagram: https://www.instagram.com/icsethiopia/