በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና በጣልያን የትብብር ልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ሲቪል ምዝገባ ስርአትን በቴክኖሎጂ የማዘመን እቅድ ፀደቀ፡፡

የጣልያን የትብብር ልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ሲቪል ምዝገባ ስርአት ለማዘመን ለሁለት ዓመት የሚቆይና ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተመረጡ በሃምሳ ሁለት ወረዳዎች የሚገኙ ዘጠና ሁለት ቀበሌዎች የሚተገበር የሲቪል ምዝገባ ስርአት በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ለመተግበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት የተውጣጣ ስትሪንግ ኮሚቴ ያወጣው እቅድ ግንቦት27/2016 ዓ.ም ውይይት ተደርጎበት መፅደቁን ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት ከአሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጲያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት፣ ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካዮች እና ከጣልያን የትብብር ልማት ኤጀንሲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ መድረኩን የከፈቱት በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወልዴ እንዳሉት፡- የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የኢትዮጵያ ሲቪል ምዝገባ ጥራትና ሽፋን ለማጠናከር ከባለድርሻና አጋር አካላት ተቀናጀቶ በርካታ ሪፎርም ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በጣልያን የትብብር ልማት ኤጀንሲ ድጋፍ የተቀረፀው ፕሮጀክትም የሲቪል ምዝገባ ስርአትን ወደ ተናባቢ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ሂደት ለማስገባት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም ሁሉም የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡ 

በጣሊያን የትብብር ልማት ኤጀንሲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ፌበን ጌታቸው በበኩላቸው ኢጄንሲያቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ምዝገባ ስርአት ለማዘመን የጀመረው ድጋፍ አጠናከሮ እንደሚቀጥልበት ተገልፀዋል፡፡

የወጣው እቅድ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ናትናኤል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት መፅደቁን ታውቋል፡፡