የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች  የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት  አደረጉ።

የውይይት መድረኩን የከፈቱት የኢሚግሬሽና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር  ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተቋሙ የሪፎርም አመራር ባለፈው አመት በዚሁ ወር ሥራ ሲጀምር በተቋሙ የነበሩ ችግሮች በርካታና ውስብስብ መሆናቸውን ከተገነዘበ በኋላ በተለመደ አካሔድ ሳይሆን   ሁለንተናዊ እና ስልታዊ  ሪፎርም እንደሚያስፈልገው አረጋግጦ 11 የሪፎርም አጀንዳዎች በመቅረፅ በበጀት አመቱ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ገልፀዋል።

አክለውም በወቅቱ የነበሩ ችግሮችን አመራሩ  በፈጠረው ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርና ባስቀመጠው አቅጣጫ ለመፍታት እንደተቻለ አስረድተዋል፧ በተለይ የፓስፖርት እጥረትን ተከትሎ የፓስፓርት አገልግሎት  ቆሞ እንደነበረና አመራሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት 1.5 ሚሊየን የፓስፓርት ቡክሌቶችን ወደሀገር ውስጥ በማስገባት 1.1 ሚሊየን ፓስፓርቶችን በማተም ለረዥም ጊዜ ይጠባበቁ ለነበሩና ለአዲስ አመልካቾች መስጠት እንደተቻለ ገልፀዋል። 

በኢሚግሬሽን ታሪክ በአመት ትልቁ ቁጥር  360 ሽህ ፓስፓርት ይታተም እንደነበረና በዘንድሮ  አመት 1.1 ሚሊየን ፓስፓርት መታተሙ ትልቅ እምርታ መሆኑን አስረድተዋል።

በሪፎርሙ አጀንዳዎች ከሕግ ፣ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀት፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከሰው ሃይልና ከፋይናንስ  አንፃር የነበሩ ችግሮችን በመሰረታዊነት መፍታት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ለመከናወን እንደተቻለ አስረድተው በተለይ የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅና የኢሚግሬሽን አዋጅ መፅደቃቸው ተቋሙ የነደፋቸው የሪፎርም አጀንዳዎችን ለማስፈፀም ትልቅ ጉልበት እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

የተመዘገቡ ውጤቶች መንግስት ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሰጠው ትኩረት፣  ባለድርሻ አካላት ያደረጉት ድጋፍና የተቋሙ ሰራተኞች ያሳዩት ተነሳሽነት መሆኑን ገልፀው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አክለውም የተጀመሩ የሪፎርም አጀንዳዎችን ሙሉ በሙሉ በመተግበር  በ2016 ዓ.ም የተስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም የተመዘገቡ እምርታዎችን በማጎልበት  መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የ2016 ዓ/ም እቅድ አፈፃፀም ሪፓርት እና የ2017 ዓ/ም  እቅድ ወደ መድረክ ቀርቦ በሰራተኞች ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ስብሰባው ተጠናቋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133