የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ29ኛ መደበኛ ስብሰባው ሶስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/9 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ረቂቅ አዋጁ ለዜጎችና ለውጭ አገር ዜጎች የጉዞ ሰነድ፣ ህጋዊ የይለፍ ፈቃድ ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ለመስጠት፣ በህግ የተከለከሉ ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡና ወደ አገር እንዳይግቡ ቁጥጥር በማደረግ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመቆጣጠር የሀገርን ብሔራዊ ደህንነትና ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡



ምክር ቤቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 354/9 ማሻሻያ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 19/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ከተቀመጡት መሰረታዊ መብቶች አንዱ የሆነውን የዜጎችን የመዘዋወር ነፃነት ማስከበር ያስችል ዘንድ ለኢትዮጵያውያንና ለውጭ አገር ሰዎች ሕጋዊ የጉዞ ሰነድና ቪዛ ለመስጠትና ለማረጋገጥ እንዲሁም ብሔራዊ መታወቂያን በመስጠት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 20/2016 አድርጎ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ አጭር ማብራሪያ የሰጡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ለማድረግ ሲሆን የአፈፃፀም ስልቱ ህገ-መንግስቱን መሠረት ያደረገና ዘለቄታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችና አሰራሮች በሁሉም ዘርፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባን አስመልክቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 21/2016 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የተመሩትን ረቂቅ አዋጆች ካላቸው ሀገራዊ ፋይዳና ጠቀሜታ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ያላቸውን መስተጋብር ቋሚ ኮሚቴዎቹ ትኩረት ሰጥተው በዝርዝር እንዲያዩት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
