አዲስ አበባ፡ 27/09/2017 ዓ.ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የታይላንድ ሙሉ አምባሳደር ማራኮት ጃኔማትኮርን በቢሯቸው ተቀብለው በህዝብ ለህዝብ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ታይላንድ በተለየ ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን የመዳረሻ ቪዛ እንደሰጠች የገለፁት አምባሳደርዋ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እየተደረገላቸው ላለው መልካም አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የህዝብ ለህዝብ ትብብር ቅድሚያ እንደሚሰጠው እና በዚህ ረገድ አገልግሎታችን ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተርዋ ተቋሙ በለውጥ ስራዎች ላይ እንዳለ እና በአየር መንገድ የሚሰጠው አገልግሎት መሻሻሎች እንዳሉት በውይይቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡
የአገልግሎቱ የኢሚግሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በበኩላቸው ተቀራርቦ መስራት ለሁላችንም መልካም ሲሆን ግንኙነቱ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቶሎ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ እና ታይላንድ መካከል ከ60 ዓመት በላይ መልካም ግንኙነት መኖሩ ተገልፆ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
