ኢትዮጵያ የአለማቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ቁልፍ የህዝብ መረጃ ልውውጥ ስርዓት የአባልነት ማረጋገጫ ተቀበለች 

የኢትዮጵያ 105 አገራት ባቀፈው የአለማቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ቁልፍ የህዝብ መረጃ ልውውጥ ስርዓት (PKD) አባል መሆኗን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ከተቋሙ ዋና መቀመጫ ከሆነችው ካናዳ ሞንተሪያል ተቀብላለች።የማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የዓለማቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዝዳንት፣ የካናዳ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎችም የድርጅቱ ከፍተኛ ሃላፊዎችና የአገራት ተወካዮች፣  የኢንሳ  ዋና ዳይሬክተር እና በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በተገኙበት ተረክበዋል። 

ኢትዮጵያ የዚህ ማዕቀፍ አባል መሆኗ የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በአባል አገራቱ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ያለምንም እንግልት እንዲጓጓዙ የሚያስችል ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ በየብስም ሆነ በአየር  በተጭበረበረ  የጉዞ ሰነድ ለመምጣት የሚሞክሩ አካላትን በቀላሉ ለመለየት የሚረዳና በአገር ላይ ሊቃጣ የሚችል የደህንነት ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ ነው። 

ኢትዮጵያ ወደ ዚህ ማዕቀፍ በይፋ መቀላቀሏን ተከትሎ የአለማቀፉ አቪዬሽን ድርጅት አባል አገራት ተወካዮችና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች አካላት በተገኙበት አገሪቱ ያላትን ሁለንተናዊ አቅም የሚያስተዋውቅ መድረክ ተዘጋጅቷል። በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ገፅታ፣ የኢሚግሬሽን ስርዓትና አሁናዊ ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያን የቱሪዝምና የቢዝነስ አቅሞች የሚያስተዋውቁ ገለፃዎች ተደርገዋል። 

በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ኢትዮጵያ የዚህ ማዕቀፍ (PKD) አባል መሆኗ ዜጎች በሚሄዱበት አገር ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረጉ ባሻገር የአገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ጠንካራ በሆነው የአለም አቀፍ አቪዬሽን ትብብር ስርዓት ውስጥ የላቀ ቴክኖሎጂን መጠቀሟ  ድንበሯን ከመጠበቅ ባለፈ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ደኅንነት መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነትም የሚያሳይ ውሳኔ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የካናዳ ትራንስፖርት ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ኒኮላስ ሮብሰን በበኩላቸው

ኢትዮጵያ ወደዚህ ስርዓት በይፋ መቀላቀሏ በአቪዬሽን መስክ የምትሰራውን ስራ በዓለም የታመነ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።በተለይም በርካታ ዜጎችን ወደ ተለያዩ ክፍለ-ዓለማት የሚያጓጉዝ የግዙፍ አየር መንገድ ባለቤት በመሆኗ ይህን ማዕቀፍ መቀላቀሏ የሚደነቅ ውሳኔ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የአለማቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ፕሬዝዳንት ሳልቫቶሬ ሻኪታኖ ኢትዮጵያ ወደ ማዕቀፉ በመግባት የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ተቋማቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

——

Telegram: https://t.me/ICS_Ethiopia

Facebook: https://www.facebook.com/ICSEthiopia

Twitter: https://twitter.com/ics_ethiopia

TikTok: https://www.tiktok.com/@ics_ethiopia

LinkedIn: https://www.linkedin.com/company/icsethiopia

YouTube: https://www.youtube.com/@Ics_Ethiopia

Instagram: https://www.instagram.com/icsethiopia/

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133