ህዳር 08/2018 ዓ.ም
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን የ2018 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ ግማሽ ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት ለዜጎች በመስጠት እንዲሁም በትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ፣ በቪዛ እና ሌሎች የይለፍና የጉዞ ሰነዶችን ለደንበኞች በመስጠት ረገድ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸዉን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ ከ545ሺ በላይ ፓስፖርት ለዜጎች መሰጠቱን የገለጹት ወይዘሮ ሰላማዊት አገልግሎቱ የዲጂታል አገልግሎትን በማሻሻል እንዲሁም የፓስፖርትና ቪዛ ስርዓት በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ለዜጎች በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ነዉ የተናገሩት።
ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ከቪዛ አገልግሎት ጋር ተያይዞም 321ሺ በላይ ቪዛ ሰጥቷል። ከዚህም ባለፈ 11,250 ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ እንዲሁም 5,161 የውጭ አገር ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በመስጠት የተሳካ የእቅድ አፈፃፀም ማስመዝገቡምንም ጠቅሰዋል ዋና ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸዉ።
በአየር እና በየብስ ድንበር አለማቀፍ ስታንዳርዶችን በጠበቀ መልኩ በጉዞ ሰነድ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱም ነው የተጠቀሰው።
ከአገልግሎት ተደራሽነት በተጨማሪ የውጭ ዜጎችን እና የድንበር ቁጥጥር ስራ በማጠናከር የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት ለመጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴዎቹ ያብራሩት ወይዘሮ ሰላማዊት በሩብ አመቱ 860 ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው ፖስፖርት ለመውሰድ የሞከሩ የውጭ ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር አውሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን መቻሉንም በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በ2018 ዓ.ም በአንደኛ ሩብ ዓመት አስራ አንድ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገልጸዋል። ይህም ከዕቅዱ 96 በመቶ በላይ ማሳከት መቻሉን በሪፖርታቸዉ ጠቅሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴዉ አባላትም ከአገልግሎት ተደራሽነት፣ ስራዎችን በቴክኖሎጂ የታገዙ ከማድረግ፣ የአገልግሎት ፈላጊዎችን እርካታ እዉን ከማድረግ፣ ከሰዉ ሃይል አቅም ግንባታ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷል።
የቋሚ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የዜጎችን መብት በጠበቀ መልኩ ጊዜዉን የዋጁ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን በመክፈትና ተደራሽነትን በማሳደግ እና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የአገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና ለማሻሻል የሚያደርገዉ ጥረት ሌሎች ተቋማት አርዓያ መሆን የሚችል በመሆኑ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲሱን የኢፓስፖርት ሲስተም ወደ ክልሎት ማስፋት ፣በሃሰተኛ ሰነድ አገልግሎት የማግኘት ሙከራ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ፣ አልፎ አልፎ የሚያጋጥምን የኔትዎርክ መቆራረጥ መፍትሄ ማበጀት እንዲሁም የድንበር አስተዳደር ማዘመን እና ዘመናዊ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን መዘርጋት አገልግሎቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራባቸዉ አሳስበዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
