የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ከዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የፋይዳ መታወቂያን ለፓስፖርት አገልግሎት እንደ ቅድመ ሁኔታ ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ የተዘጋጀ የሚዲያ መግለጫ

የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው የፖስፖርት አገልግሎቶች የፋይዳ መታወቂያን ከሚስፈልጉ ዋና ሰነዶች በማካተት ፣እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ከዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በትብብር ለመስራት ከስምምነት ተደርሷል።

የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከዚህ ቀደም የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር ከሰኔ 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የፋይዳ መታወቂያን ለፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ቅድመ ሁኔታ ለማድረግ  መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በጋር በመሆን ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቆ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የምትመራበት የኢኮኖሚ ፖሊስ፤የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ 2 እና በዲጂታል ስትራቴጂ 2025 መሠረት የተሰጠው ቁልፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘንግ ነው፡፡ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አስቻይ ከመሆኑም ባሻገር የነዋሪዎችን ባዮሜትሪክ መረጃ በመውሰድ ግለሰቦችን በልዩነት በመለየት ተቋምን ከተቋም፥ ከተማን ከክልል፣ከተማን ከከተማ በማሰናሰል፤ የመታወቅ ስርዓትን በማረጋገጥ፤ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተተገበረ ያለ ስርዓት ነው። በዚህም አግባብ፣ በቀዳሚነት በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለፖስፖርት አሰጣጥ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ በማድረግ በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ደህንነታቸውን የጠበቁ፣ እንዲሁም ተደራሽ ለማድረግ ከዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ተደርሷል። 

ይህም የጋራ ትግበራ የዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም እና የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ማንነትን በማጭበርበር የተለያዩ ሰነዶችን ለማግኘት የሚደረግን ጥረት ለመግታት የሚያስችል መሆኑን ታምኖበታል። በመሆኑም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የፓስፖርት አገልግሎት ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ግለሰቦች ፓስፖርት ለመውሰድ ሲመጡ በቅድሚያ በፋይዳ ተመዝግበው ልዩ ቁጥር ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን ተገልጋዮች የፋይዳ መታወቂያቸውን በወረቀት መልክ አሳትመው ወይም ዲጂታል ኮፒውን ይዘው በስልካቸው ይዘው በመምጣት ብቻ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እናሳውቃለን፡፡ ተገልጋዮች በወረቀት ላይ የታተመ የፋይዳ QR ኮድ ወይም በስልካቸው የዲጂታል ኮፒውን ሲያቀርቡ የአገልግሎቱ ባለሞያዎች የመታወቂያውን ትክክለኛነት በመተግበሪያ በማረጋገጥ  አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል፡፡

ይህ የጋራ ትግበራ ጅማሮ ሲሆን የፋይዳ መታወቂያን በአገልግሎቱ ከሚለሙ ስርዓቶች ጋር በማስተሳሰር የፋይዳ ስርዓትን ከሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት፣ ከመኖሪያ ፍቃድ ስርዓት፣ ከትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ስርዓት ጋር የማስተሳሰር ስራ የመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ እቅድ እንዲሆኑ ተቋማቱ ተስማምተዋል፡፡ 

የፋይዳ መታወቂያን ቅድመ ሁኔታ መሰረት ያደረገ የፖስፖርት አሰጣጥ ትግበራ ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ የጋራ ግብረሃይል አቋቁመው፣ የእቅድ ዝግጅት እና የቅድመ-ትግበራ ሥራዎችን ጀምረዋል። በዚህም ትግበራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በመላ ሀገሪቱ የተቀናጀ አገልግሎት አሰጣጥን ይተገብራሉ፡፡ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያቸውን በወረቀት መልክ ባሉበት ለማተም እና አገልግሎት ላይ ለማዋል resident.fayda.et ላይ በመግባት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያቸውን በግላቸው ማተም የሚችሉ ሲሆን በአማራጭ ተገልጋዮች የፋይዳ መታወቂያ መተግበሪያን ከ id.et/app ላይ በማውረድ ዲጂታል መታወቂያውን በማግኘት አገልግሎት ማግኘት ይቻላሉ፡፡ 

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እና ዲጅታል መታወቂያ በቅንጅት በመስራት ለዜጎች አገልግሎት ቅልጥፍና፣ የስራ ድግግሞሽን እና የሀብት ብክነትን የሚያስቀር ሲሆን ተቋማት ተናበው እንዲሰሩ በማድረግ፣ በፋይዳ መታወቂያ ዙሪያ የዲጂታል ስነ-ምህዳር በመገንባት እንዲሁም የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎቶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የዲጂታል ዘመንን የዋጁ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ በማድረግ በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ምንዳው ከፍተኛ ነው።

ለበለጠ መረጃ በድህረ ገጽ ics.gov.et እና id.gov.et ማግኘት ይችላሉ፡፡

ሚያዚያ 18 ቀን 2017 .

አርባምንጭ፤ኢትዮጵያ

Latest Posts

Any Questions?

Call us!

8133